ኢትዮጵያ ትግራይን እየገፋች ነው፦ ከታሪክና ትውስታ የመፋቅ ዓላማ ይዞ የመጣው ጦርነት፣ የተፈፀሙት አረመንያዊ ወንጀሎች እና ተዛማጅ ክህደቶ ያነጠፉት አስገዳጅ ፍቺ

ኢትዮጵያ ትግራይን እየገፋች ነው፦ ከታሪክና ትውስታ የመፋቅ ዓላማ ይዞ የመጣው ጦርነት፣ የተፈፀሙት አረመንያዊ ወንጀሎች እና ተዛማጅ ክህደቶ ያነጠፉት አስገዳጅ ፍቺ
በትግራይ ነፃነት ድምፆች ወይም Voice for Independent Tigray የተዘጋጀ
01/27/2026
በ1935 ገደማ በትግራይ የንጉሱን ጨቋኝ አስተዳደር በመቃወም “ወያኔ” በመባል የሚታወቀው የገበሬዎች ዓመፅ ተነስቶ ነበር። ወያኔዎቹ በተከታታይ ውጊያዎች መቐለን እስከመቆጣጠር የደረሱ ድሎች ተጎናፅፈው ነበር። ንጉሱ የእንግሊዝ ጦር አውሮፕላኖች በመጠቀም ከየመን በመነሳት ገበያ በተሰበሰበ ህዝብ ላይ ቦንብ በማዝነብ በሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ጨፍጭፈው ነበር ተቃውሞውን የተቆጣጠሩት። ምንም እንኳን አመፁ የገበሬዎች ቢሆንም፣ ያኔም የወያኔዎቹ መሪ ቃል፤ “ሕግና ሕጊ ገረብ፣ ባንዴራና ናኢትዮጵያ” (ህጋችን የራሳችን፣ ባንዴራችን የኢትዮጵያ) የሚል ነበር። ከአውሮፕላን ጭፍጨፋውም በኋላ መሪ ቃሉ ላይ የሰፈረው ለባንዴራው የነበረውን ታማኝነት የሚቀይር አመለካከት አልተሰማም።
በ1967 ዓ/ም ሁለተኛውን ወያኔ፣ በገበሬዎች ሳይሆን በተራማጅ ተማሪዎች የተመራ የትጥቅ ትግል የተጀመረበት ወቅት ነው። ታጋዮቹ በደደቢት በረሃ ቆይተው ከህዝብ ጋር ለመቀላቀልና ለመተዋወቅ በሃምሌ ወር ወደ ደጋ ሲንቀስቀሱ የገብርኤል አመት ንግስ ለማክበር ገዳም ላይ ከተሰበሰበ ህዝብ ጋር ይገናኛሉ። ከብዙ ህዝብ ጋር ሲገናኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የፖለቲካ ዓላማቸውን ሲያስተዋውቁ፣ ዓላማችን ከሁሉም ኢትዮጵያን ጋር በእኩልነት የተመሰረተ ስርዓት ካልሆነም ነፃነት ነው ሲሉ፣ አንዱ ቄስ ብድግ ብለው “የመጀመሪያው ይሻላል እንጂ፣ ትግራይ እኮ የአገር መሰረት ናት። የጎጃም፣ የሸዋ ሲባል እንጂ፣ ትግራይ ውስጥ ከኢትዮጵያ ያነሰ ንጉስ ኖሮን አያውቅም፣ የትግራይ ንጉስ ሲባል ሰምተን አናውቅም፣” ሲሉ ታጋይ-ተማሪዎችን ሞገቱ። የህዝቡ ስሜት ካዩ በኋላ፣ መጀመሪያ ላይ በተወሰኑ ዘንድ ሲቀንቀን የነበረው፣ ትግራይ ሪፓብሊክ የሚለውን አጀንዳ ቀርቶ፣ የኢትዮጵያን ስርዓት ማስተካከል ወደሚለው ቅኝት ተስተካከለ።
ለረጅም ጊዜ በነበረው ዘመናዊ የፖለቲካ ትርክት፣ በትግራይ እና በኢትዮጵያ የወደፊት ግንኙነት ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች በተሳሳተ መንገድ ሲገለጹ ቆይተዋል። አብዛኛው ትርክት ትግራውያን ስለ መገንጠል እያሰቡ እንደሆነ፣ ወይም የኢትዮጵያን መንግሥታዊ አንድነት ለመተው እያማተሩ እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል። ይህ አገላለጽ አሳሳች ብቻ ሳይሆን፣ ፍፁም ቅጥፈት ነው።
ከዚህ ከእውነት ጋር ከተጣላ ትርክት በስተጀርባ ያለው እውነታ እጅግ አደገኛና የተወሳሰበ ነው። ራስን የማጥፋት ሂደት ነው። የአንድነትን ሰንሰለት በስልት እየበጣጠሰች ያለችው ኢትዮጵያ እንጂ ትግራይ አይደለችም። ትግራይ ላይ በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀልና ክህደት ምክንያት አንድ ቀን ትግራይ የመለየትን መንገድ ብትመርጥ፣ ታሪክ ይህንን ምርጫ እንደ ቅንጦት ወይም አመፅ አይቆጥረውም። ይልቁንም እንደ ብቸኛ ለትግራይ የቀረላት የመትረፊያ መንገድ ወይም ህልውናን ማስቀጠያ እንጂ።
ነፃነት ከርዕዮተ-ዓለም ብቻ የሚወለድ አይደለም። ከአብሮነት ስብራት፣ ከመበደል ልምድ፣ ከቁስል፣ ከክህደት እና በአንድ የፖለቲካ ማህበር ውስጥ መቀጠል ውርደትን፣ ጥፋትን እና መደምሰስን ብቻ እንደሚያመጣ ከመገንዘብ የሚወለድ ነው። በትግራይ ረገድ፣ ወደ መለያየት ለሚወስደው መንገድ እያንዳንዱን ድንጋይ የነጠፈችው ራሷ ኢትዮጵያ ናት።
በዘር ማጥፋት ጦርነት የፈረሰ አንድነት አይናችን ጨፍነን ሳይሆን ፊለፊት አፍጠን እናየዋለን። ለዚህ የዘመኑ ግዙፍ ሃጥያት ሌላ ይቅር መባባያ መንገድና ስርየት የለም። ኢትዮጵያ በእውነት ትግራይን የምትፈልጋት ቢሆን ኖሮ፣ እሷን ለማጥፋት የታለመ ጦርነትን በጭራሽ ባልከፈተችባት ነበር።
ከጥቅምት 2013 ዓ.ም በኋላ በትግራይ ላይ የተፈጸመውን ድርጊት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ልዩነት፣ የሕገ-መንግሥት ክርክር ወይም የሊቃውንት ሽኩቻ ሊያጸድቀው አይችልም። የኢትዮጵያ መንግሥት የታጠቀ ቡድንን ብቻ አይደለም የተዋጋው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን የገደለ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ያፈናቀለ እና ሙሉ ማህበረሰብን ወደ ፍርስራሽ የለወጠ ዘመቻ ለማካሄድ ሙሉ አገራዊ እና ወታደራዊ አቅሙን፣ ያውም ከባዕድ ጦር ጋር በመሆን ያዘመተ አገዛዝ ነው። ለዘመቻውም ከልሂቃኑና ተቋማቱ ከጠየቀው በላይ ድጋፍ ተችሮታል።
የአንድን አካባቢ ባለቤትነት የሚጠይቅ መንግሥት ውጫዊ ጠላትን ጋብዞ ግዛቱን እንዲያረክስ አያደርግም። ነገር ግን ኢትዮጵያ የኤርትራን ጦር ወደ ትግራይ ከመጋበዝ ባለፈ፣ በጅምላ ግድያ፣ በስልታዊ አስገድዶ መድፈር፣ በባህላዊ ውድመት እና በሰፊ ዝርፊያ ሲሳተፉ በቅንጅት ሰርታለች፣ በገንዘብ ረድታለች፣ በዲፕሎማሲም ከለላ ሆናለች።
ኢትዮጵያ ትግራይን ብትፈልጋት ኖሮ፣ ወደ አረመንያዊ የእልቂት ሲኦል ባልቀየረቻት ነበር።
የዘር ማጥፋት በጦርነት መሃል የሚከሰት አጋጣሚ አይደለም፤ የፖለቲካ ውሳኔ እንጂ። የጥቃቱ ስፋትና ቅንጅት፣ ሲቪሎችን ሆን ብሎ ማጥቃት፣ የሆስፒታሎች፣ የትምህርት ቤቶች፣ የእርሻ ቦታዎች፣ የአብያተ ክርስቲያናት እና የቅርሶች መውደም ሁሉም ወደ አንድ አስፈሪ ድምዳሜ ያመለክታሉ፤ ግቡ ማሸነፍ ሳይሆን ማጥፋት ነበር። እንዲህ ዓይነት ድርጊት የተፈጸመበት አንድነት ፈጽሞ ሊቀጥል አይችልም። ያውም የተጎዳውን ማከም፣ ለሆነው መጸጸት፣ እንባን ማበስ በሌለበት ሁኔታ ፈፅሞ የሚፈለግም፣ የሚታሰብም አይሆንም።
የፀፀት አለመኖር፤ ሁለተኛውና ዋነኛው አይረሴ ወንጀል ነው። ጦርነቶች፣ ፍትሃዊ ባልሆኑበት ጊዜ እንኳ፣ አንዳንድ ጊዜ እርቅና ፈውስ ሊከተላቸው ይችላል። ነገር ግን ፈውስ ፀፀትን፣ ተጠያቂነትን እና መልሶ ማቋቋምን ይጠይቃል። ኢትዮጵያ ግን ከእነዚህ ውስጥ አንዱንም አልመረጠችም።
የጥይት ድምፅ ሲቀንስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይን ለመገንባት አልሞከረም። ይልቁንም ረጅም ጊዜ የፈጀ እገዳ በመጣል ምግብን፣ መድኃኒትን፣ የባንክ አገልግሎትን፣ ኤሌክትሪክን፣ ቴሌኮሙኒኬሽንን እና ነዳጅን ከለከለ። ረሃብ ፖሊሲ ሆነ፤ መከልከል ደግሞ ስልት።
ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላም ቢሆን ስቃዩ አላበቃም። የምዕራብ ትግራይ መሬቶች አሁንም እንደተያዙ ናቸው። ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው መመለስ አልቻሉም። ሺዎች አሁንም በእስር ላይ ናቸው። መሰረታዊ አገልግሎቶች የተመለሱት በከፊል ነው። የሰብአዊ እርዳታ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ሆኗል። መልሶ ግንባታውም ተጓትቷል ሳይሆን እሱ ሳይጀመር የሚወራው ስለ መልሶ ማውደም ነው።
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ የሞራል ተጠያቂነት አለመኖሩ ነው። ምንም ዓይነት አገራዊና ዓለማቀፋዊ፣ ወይም ከሁለቱም የተውጣጣ ምርመራ አልተደረገም፣ ከፍተኛ አጥፊ ባለሥልጣናት አልተቀጡም፣ ይፋዊ ይቅርታ አልተጠየቀም። በተቃራኒው ተጎጂዎችን ያፌዙ ባለሥልጣናት አሁንም በሥልጣን ላይ ናቸው። ትግራውያንን "ከምድር ገጽ እናጠፋለን" ብለው ተግባር ላይ ያዋሉት፣ ከ150,000 በላይ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የደረሰውን አስገድዶ መድፈር ያቀለሉ ድምፆች አልተገቱም፤ ይልቁንም እንደ ተራ ነገር ተቆጠሩ።
የሞቱብህን ለማልቀስ አሻፈረኝ የሚል መንግሥት፣ ያንተን ወገንተኝነት አስቀድሞ የቀበረ ነው። እዚህ ላይ አንድ የታወቀ፣ የኢትዮጵያን ስም ግንባታ ላይ ብዙ የሰራ የትግራይ ምሁር፡ “የጋራ ሃዘን የሌለው ህዝብ፤ የጋራ አገር አለኝ ቢል ቧልት ነው” ያለውን ያስታውሷል፤፡
በቁስል ላይ መላገጥ፤ የትግራይ ውድመት ፖለቲካዊ ትርፍ ብለው ያመኑ ግብዛን ጥቂት አይደሉም።ከጦርነቱ በኋላ የታየው ነገር የበለጠ ጨለማ ነው። የትግራይ መጎዳት ለፖለቲካ ትርፍ ማግኛ የሚፈለግ ሆኖ አይተናል። ሊቃውንት እና ተቋማት በትግራይ መፈራረስ አልተሰቃዩም፤ ይልቁንም ከውድመቱ ተጠቃሚ መሆንን ተማሩ። የትግራይ ፍርስራሽ ለድርድር መጫወቻ ሆነ። በትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ክፍተቶች መጠቀሚያ ሲሆኑ ታዝበናል። በዘመኑ ባለስልጣናት ዘንድ ትግራይ በጭራቅነት ማስፈራሪያ፣ አለያም እንደ ትግራይ ትቀጠቀጣላቹህ፣ ትደቃላቹህ፣ ትበሽሻላቹህ በሚል ማስፈራሪያነት ስትጠቀስ በተደጋጋሚ ሰምተናል።
ይህ የአንድነትና አብሮነት ወግ አይደለም፤ ይህ በባርነት ግዛት ስር የማንበርከክ ተግባር ነው።
ወርቁን በጠጠር የመለሰ የታማኝነት ታሪክን በክህደት የመለሱ የኢትዮጵያ ተቋማት ገዢዎችና ልሂቃን ይህ አሳዛኝ ክስተት በታሪክ መነፅር ሲታይ ደግሞ የበለጠ ይመራል። ለዘመናት ትግራይ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ እና አገራዊ ማንነት ማእከል ሆና ቆይታለች። አክሱምም አድዋም፣ ፅዮንም አልነጃሽም የሚገኙት ትግራይ ውስጥ ነው። ትግራይ ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ መሠረት ጥላለች። የትግራይ አርበኞች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስጠብቀዋል።
ይሁን እንጂ ትግራይ ለዚህ ውለታዋ ክብር ተሰጥቷት አያውቅም። በተደጋጋሚ መገለል ቢደርስባትም፣ ትግራይ መገንጠልን ተከትላ አታውቅም። የሚገርመው መለየትን ወይም ከሌላ ጋር መሆንን ለማሳካት የተሻለ ዕድል የነበረበት አጋጣሚ ብዙ ነበር። ትግራይ ግን የኢትዮጵያን አንድነት በቁርጠኝነት ስትጠብቅ ቆይታለች። በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችል አስረጅ ቁጥር የለውም።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ተቋማቱ፣ እንዲሁም ልሂቃኑና መንጋው እሷን ለማጥፋት እስኪወስኑ ድረስ ትግራይ ፀንታ ቆይታ ነበር። ጥያቄው፣ መንግሥትና ደጋፊ መንጋ ልህቃኑ በገዛ የአገረ መንግስታዊ ዋነኛ መሠረታቸው ላይ፤ ከምድረገጽ የሚያስወግድ አጥፊ መሣሪያ መጠቀምን ለምን መረጡት፣ የሚለው ነው።
በትግራይ ላይ የተከፈተው ጦርነት የኢትዮጵያ መንግሥት የሞራል ውድቀትን ያሳያል። ሕገ-መንግሥቱ ሲፈለግ እንደ መሣሪያ ጥቅም ላይ ዋለ፣ በማይፈለግበት ጊዜ ደግሞ ተጣለ። አንድን መስራች ሕዝብ ለማጥፋት ሙሉ ኃይሉን የሚጠቀም መንግሥት፣ የዚያን ሕዝብ ታማኝነት የመጠየቅ የሞራል ብቃት የለውም።
በአንድ በኩል ትግራይ ላይ የከፉና የበዙ በደሎች በመፈፀም ማድቀቅ፣ ማሳቀቅና ማራቅ የሚል አቅጣጫ ተይዞ፣ እንዲያውም “ለምን ትረሳላቹህ፣ ሂዱ እንጂ፣ ህገመንግስቱ እኮ የመሄድ መብት ይሰጣል” በሚል አስታዋሽነት እየተነገረህ፣ ትግራይ ከመንግስታዊ መዋቅርና ተሳትፎ ውጭ ሆና በመንግስታዊ ማነቀዎች እንድትማቅቅ ሆን ተብሎ በስልትና እቅድ፣ እና የሁሉም ተቋማትና ልሂቃን ይሁንታ ተችሮት ይሰራበታል። በአንድ በኩል ትግራይን ገፍቶ ብቻ ሳይሆን ገፍትሮ ማስወጣት፣ በሌላ በኩል ለመውጣት ስታስብ ደግሞ መልሶ መውቀስና መክሰስ የመሰለ ብካይ ስልት፣ ምን ይሉታል?!
አሁን ላይ የሚታየው እጅግ አስቂኝና አዲስ ነገር የኢትዮጵያ መሪዎች ትግራውያንን "ከአንድነቱ ውጡ" እያሉ መናገራቸው ነው። ትግራይን ያፈራረሰ መንግሥት አሁን ደግሞ በትግራይ የመገንጠል እድል ላይ ቅር የተሰኘ ይመስላል ሳይሆን ያስመስላል።
ቤትን አቃጥሎ፣ ጉድጓድን መርዞ፣ ቤተሰብን ጨርሶ፣ የተረፉትን ከብቦ፣ በስቃያቸው አላግጦ፣ ከመንግሥታዊ መዋቅር አውጥቶ፣ በመጨረሻም ሌላ መጠለያ በመፈለጋቸው "ከዳተኞች" ማለት አገራዊ መልክና ደረጃ የያዘ የፖለቲካ ማጭበርበር ነው። መሪዎቹን የሚያስጨንቃቸው የትግራይ መለየት ሳይሆን፣ ትግራይ አንድ ቀን አገግማ ፍትሕን ትጠይቃለች የሚለው ስጋት ነው። ትልቁን ቁምነገር ከቁብ ሳይቆጥሩ፣ ጥቃቅን ሰበቦች ላይ ይንጠለጠላሉ። ከመለያየት ይልቅ ትውስታን ይፈራሉ።
የኢትዮጵያውያን አገር ወዳድና ተራማጅ ልሂቃን መገንዘብ ያለባቸው ምንድነው?
አሁንም በፍትሐዊነት እና በብዝሃነት የምታምን ኢትዮጵያን የሚመኙ የህሊና ድምፆች ይኖራሉ። ለእነሱ አንድ መራራ እውነት መነገር አለበት። ለትግራይ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ሁኔታዎችና ግፊቶች የተፈጠሩት በመቐለ ሳይሆን በአዲስ አበባ ነው። ማንም ሕዝብ መበታተን ስለሚወድ መለያየትን አይፈልግም። ሕዝቦች መለያየትን የሚፈልጉት በአንድነት ውስጥ መቆየት ከመጥፋት ጋር እኩል ሲሆንባቸው ብቻ ነው።
አንድ ቀን ትግራይ ነፃነትን ብትመርጥ፣ ይህ መለይትን የመፈለግ ወይም የክህደት ተግባር አይሆንም። ይልቁንም የመደምሰስን፣ የውርደትን እና በዝምታ የመጥፋትን መንገድ የመቃወም ተግባር ይሆናል። ማንም ሰው ሌላ አካል ለፈጠረው "አንድነት" ሲል አልሞትም የሚልን ሕዝብ ሊወቅስ አይገባም።
ማጠቃለያው፣ አንድነት በጅምላ መቃብር ላይ ሊገነባ አይችልም፣ የሚል ነጥብ ነው።
አንድ አገር የራሱን ሕዝብ እያጠፋ የዚያ አካባቢ ባለቤት ነኝ ሊል አይችልም። ዘር ማጥፋት የፈጸመ መንግሥት ታማኝነትን ወይም አብሮነትን ሊጠይቅ አይችልም። ኢትዮጵያ በእውነት ትግራይን የምትፈልግ ከሆነ መንገዱ በኃይል፣ “በክበበው፣ አድቅቀው፣ ዋጠው” ሴራ፣ ወይም በፌዝ የሚመጣ አይደለም። መንገዱ እውነት፣ ተጠያቂነት፣ መልሶ ማቋቋም፣ ፍትሕ እና እውነተኛ የፖለቲካ እኩልነት ነው።
እስከዚያው ግን ትክክለኛው አባባል፤ ኢትዮጵያ ትግራይን እያጣች ያለችው ትግራይ መለየት ስለፈለገች አይደለም። ኢትዮጵያ ትግራይን እያጣች ያለችው እሷን ለማጥፋት ስለመረጠች ነው።
ለታሪክ ማማር ብሎ ራሱ የሚጠፋበትን መንገድ የሚመርጥ ህዝብ አይኖርም። የታሪክ ሽሚያና ክርክር ከህልውና በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይሆንም። እንደዛም ሆኖ፣ ማን ማንን እንደገፋ ታሪክ ማስታወሱ አይቀርም። ከህልውና በፊት የሚመጣ የአብሮነት ፋይዳ ሊታሰብ አይችልም፤ ምክንያቱም አብሮ መሆን፣ በህልውና ውስጥ ተኩኖ ብቻ ስለሚሆን ማለት ነው።
ፊሊስ ዲለ የተሰኘች ኣሜሪካዊት አርቲስት የትዳርን ውስብስበነት ለመጠቆም በሚል፣ በስላቅና በምፀት መልክ ከተናገረችው የሚጠቅስላት አባባል ኣለ። “እኔና ባሌ፣ ፍቺን እንዳማራጭ ፈፅመን አይተነው አናውቅም። ባይሆን ስለመገዳደል እናስባለን እንጂ።” ይላል። አባባሉ፣ የትዳር ፋይዳው አብሮነቱ የሚያመጣው ትሩፋትና ብዜት ሆኖ ሳለ፣ እሰከመጠፋፋት ዋጋ ለመክፈል፣ ማለትም ትርፉ ቀርቶ ዋናውንም የሚያሳጣ ስሌት ውስጥ ያለው ከንቱነት ለማመላከት የተሰነዘረ ጥቅስ ነው።
~//~
Recent News

Independence is the Soil, Democracy the Seed
September 14, 2025

A New Year’s Wish and Call to Unity from the Voice for an Independent Tigray
September 9, 2025

Tigray’s Independence in the Hands of Youth
September 3, 2025

Ethiopia’s Fault Lines and the Rising Call for Tigray’s Independence
September 3, 2025
